በ Libaro
ክፍል አንድ
መግቢያ
መቋጫው በሚል ርዕስ አቶ ልደቱ አያሌው አንድም ባለፉት አራት ዓመታት የሃገራችንን ውቅታዊ ሁኔታ በሚመለከት ለህዝብ ያቀረቡዋቸውን መጣጥፎች በአንድ ሸክፎ ለሚይዘው ቀጣይ መጻህፋቸው መደምደሚያ፤ሁለትም ከፊታችን ያለውን የጋራ ትግል በምን ዓይነት የትብብር መንፈስ እና የጋራ አሰተዋፅኦ ሊመራ እንደሚገባው የሚተነትን ጽሁፍ አጋርተዋል፡፡ ለማስታወስ ያክል ስድስቱ አንኳር የተነሱት ነጥቦች በቅደም ተከተል እነዚህ ሲሆኑ አንባቢው ለመከታተል ይመቸው ዘንድ የትንተናዎቹን ዓይነት የዚህን ግብረመልስ ፀሃፊ ጥቅል ግምገማዎችን በሚያሳይ መልኩ በሰንጠረዥ ተደራጅተዋል፡፡
ከላይ በተዘረዘሩትን የአቶ ልደቱ አያሌው ጽሁፍ በዚህ መልኩ ለመገምገም የተነሳሁበት ዓለማ ሁሉን ዓቀፍ ውይይት እንዲፈጠር፤ ‘ያገባኛል’ የሚል ሁሉ ያቅሙን እያዋጣ ቢያንስ በተወሰኑ የጋራ ኣላማዎች ላይ እንዲያተኮር ካለኝ መሻት በመነሳት እንጂ ለጉንጭ አልፋ ክርክርና ጸጉር ከሚስነጠቅ አቃቂረኝነት ተነስቼ አይደለም፡፡ ግምገማው የተደራጀው በሁለት ክፍል ሲሆን የመጀመሪያው ክፍል(1) የችግር መነሻ እና የሃይል ትንተናቸውን ሲዳስስ፤ ከፊታችን ያለውን ትግል እንዴት እንጠቅልለው በሚል መንፈስ የመቋጫው ተግባራዊ መጀመሪያ ሊኖረው ሰለሚገባ መልክ በሁለተኛው ክፍል(2) ላይ የራሴን ሃሳብ በመሰንዘር ነው ጽሀፌን የምጠቀልለው፡፡
ወደ አቶ ልደቱ ፅሁፍ ግምገማ ጭልጥ ብለን ከመግባታችን በፊት ግን እንዳንድ ነገሮችን ከመግቢያው ላይ ብናስቀምጥ ለመግባባት ብዙ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡ አቶ ልደቱ የተጠቀሙባቸውን አውራ ቃላትን (keywords) ብያኔ ስላልሰጡባቸው ወይም
የወሰዱባቸውን ምንጭ ስላልጠቀሱ በትክክል ሃሣባቸውን ለመረዳት አዳጋች ሆነው አግኝቻቸዋለሁ፡፡ በተለይ ቃላቱ በሃገራችን ፖለቲካው አውድ ውሰጥ ብዙ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋሉ(overly used bordering cliche) ሲሆኑ ፍቺቸው ወደ ስርክ አገባባቸው የሚያጋድል ስለሆነ የእኔም አረዳድ ይህንን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ እንደሆነ እንዲታወቅልኝ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡ ለምሳሌ ፅንፈኝነት የሚለው ቃል በሃሳብ ገበያ ላይ ከተለመደው እና በብዙሃኑ ተቀባይነት ካለው መካከለኛ አቋም (mainstream thought) ያፈነገጠ ነገር ግን ሃሣቡን በሌሎች ላይ ለመጫን የግድ ሃይልን እንደመሳሪያ መጠቀምን (violent exteremism) የትግሉ አካል ያላደረገን አካል እንደማያጠቃልል ነው የምረዳው፡፡ በቀጥተኛ ምሳሌ ለማስረዳት፤ ኦጋዴንን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል በሰላማዊ የፖለቲካ መድረክን የሚታገል ድርጅት በሃገሪቱ ባለው የፖለቲካ ያልተጻፈ ብያኔ ፅንፈኛ ተብሎ ነው የሚገለፀውና የአቶ ልደቱ ያልተብራራ የቃሉ አጠቃቀምም ከዚህ ብዙም እንደማይዘል አምናለሁ፡፡
ሌላው ጽሁፋቸውን ስናነብ ምፅዓተ-ኢትዮጵያ ተብሎ በአጥጋቢ ሁኔታ የሃገሪቱን ወቅታዊ ፈርጀ ብዙ አጣብቂኞች እንደገለጹት አምናለሁ፡፡ ይህንንም ለማወቅ የጽሁፋቸውን የመጀመሪያዎቹን ሁለት አንቀፆች ብቻ ማየት ይበቃል፡፡ እንደውም ለሠርክ የምንደርገው በሀገሪቱ መንብር ያለብት ርዕዮተ ዓለማዊ ምርጫ ላይ መከራከርን ቅንጦት በሚያሰመስል ሁኔታ ያለፉት 5 ኣመታት እንገብጋቢው ጥያቄችን እንደሀገር የመጥፋት እና የመጠፋፋት መሆኑን በአጥጋቢ አገላለፅ አሰቀምጠውታል፡፡ ታዲያ ይህን ቢሉም በዚህ የኃይል አሰላለፍ ጽሁፋቸው ግን በተለመደው ባህላዊ የርዕዮተ ዓለም አተያይ በተጫነው መነጽር የተቃኘ ይመስላል እላለሁ፡፡ በእኔ አመለካከት የትንታኔቸው አድማስን በጥቂቱ ገረበብ አድርገው ቢተልሙት አሁን ላለንበት ትርምስ የመውጫ
መንገድ የሚያመላክት ይሆን ነበር፡፡ የአለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት በሀገሪቱ የቅርብ ጊዜ ታሪክ የተለዩ ስፍራ የሚይዙ ናቸው፡፡ በእንዚህ ዓመታት ዙሪያ ያለውን የመንስዔና ውጤት ግንኙነት ስንተነትንም ‘ነገርን ከስሩ’ ለማየት በሚል ፈሊጥ ተጠልፈን ከተማሪዎች ንቅናቄ ብንነሳ የያዝነውን ጉዳይ ያዶለዱመዋል እንጂ አያሰላውም፡፡ ነገርዬው የማይናቅ እውቀት ቢሆንም
የሚያንፅ ጥበብ መሆኑ ላይ ያከራክራል፡፡ ዛሬ ላይ የምንደርገው የወንድማማቾች ጭቅጨቅ እና ፖለቲካዊ ክርክር መከራችንን ለመቋጨት የጊዜን ዘንግ እንደመጠምዘዝ ሁኖ (resetting time to Pre-PP months)) ቢያንስ ከሲዖል ወጥተን ሳናውቅ ወዳለፍነው መስቀለኛው መንገድ ነጥብ ለመድረስ ብቻ ቢሆን እርምጃችን ቅልጡፍ ይሆናል፡፡
ሲኦል ደጃፍ ላይ ቆመን የምናደርገው የአሰላለፍ ትንተና (ትንተና 1 ተብሎበምስሉ ላይ የተገለጸው)፤የሽግግሩ መጀመርያ ወራት አካባቢ የነበረውን ዓይነት መስቀለኛው ላይ ቆመን ከምናከፋፈለው የተዋኞዮች ድርሻ ብያኔ(ትንተና 2) እጅጉን ይለያያል፡፡ዴምክራሲያዊ ባህል አቆጥቁጦ ፖለቲካችን ሲሰክን የምናደርገው ትንተና (ትንተና 3) ደግሞ ከሁለቱም ይለያል፡፡ እንዚህን ልዩነቶች ያላገናዘበ አተያይ ለጊዜው ችግር የሚመጥን የጊዜው ሁነኛ መፍትሄ ማፈላለግ ላይ እምብዛም ነው፡፡ በዚህ አኳያ በመግቢያዬ መደምደሚያ ላይ የአቶ ልደቱ ፅሁፍ የተወሰኑ ዝነፈቶች አሉት ለማለት እወዳለሁ፡፡
2- የአቶ ልደቱ ጽሁፍ ሲገመገም
አገራችን የምትገኝበት ወቅታዊ ሁኔታ ምን ይመስላል? እና በሥልጣን ላይ የሚገኘው የወቅቱ አገዛዝ ማን ነው? የማንስ ነው? በሚሉት ላይ እንደዚ በቀደሙ ሁሉ አጥጋቢ በሆነ ሁኔታ ፖለቲካውን አቶ ልደቱ ተንትነውታል፡፡ በመግቢያው ሠንጠረዥ ላይ እንደተጠቀሰው በመስማማት የሚታለፍ ጥሩ ግምገማ ስለሆነ ከተራ ቁጥር 3 በኋላ ያነሱትን ጉዳዮች ላይ
አተኩረን እንቀጥላለን፡፡
2.1. የስብራታችን መሰረታዊ ምክንያቶችስ በፀሃፊው አተያይ
እንደሳቸው አባባል በታሪክ አጋጣሚ በተከታታይ ያጋጠመን የአመራር ድክመት(ሀ)፣ እንደ ህዝብ በባህል ደረጃ ያዳበርነው የፅንፈኝነት እና ጦረኛነት መንፈስ(ለ)፣ እና በመጨረሻም የብሔርተኝነት ፖለቲካ መዋቅራዊ ገዢ አስተሳሰብ መሆን ናቸው(ሐ) ይላሉ፡፡ እስቲ የተነሱትን ሶሰት ምክንያቶች ገላጭነታቸው(1) ላይ እና ችግራችንን ለመፍታት እንዴት ሊረዱን ይችላሉ(2) በሚሉት ሁለት የግምገማ መስፈርቶች እንመዝናቸው፡፡
2.1.1. የአመራር ድክመት እንደ ምክንያት
በአንደኛ ደረጃ የጠቀሱት ችግር በዘመናት የታየው የመንግሰታት አመራር ድክመት ሀገራችን ላለችበት ውድቀት የማይናቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ለዚህም እንደማሳያ ከንጉሱ ዘመን አሁን እሰካለንብት ወቅት ድረሰ ያነበሩትንና ያሉትን መሪዎች ‘እንዲያ ቢያደርጉ’ ‘እንዲህ ቢመሩ’ የሚል ቁጭት የተጫነው የቢሆን ትንተና(scenario analysis) አስቀምጠዋል፡፡ ነገር ግን ትንተናው በተወሰነ ደረጃ ገላጭ ቢሆንም አሁን ላለንብት ጊዜ እንደ ውይይት ሃሳብ መቅረቡ በዕድላችን ከመቆጨት ውጪ ምን ማድረግ እንችላለን ያስብላል፡፡ ነገር ግን ጉዳዩን እንደ ክፉ ዕጣ ሊታይ የሚገባው፤የሚታደሉት እንጂ የማይታገሉት ነገር ነው ብለን ከማለፍ ይልቅ፤ ‘እነዚህን መሪዎች የፈራ ህብረተሰብ ምን ዓይነት የወል ችግር ቢኖርበት ይሆንን?’ ብሎ መገምገሙ ከመነሻችን እንዳልነው ውይይታችንን የበለጠ ፋይዳ-ተኮር ያደርገዋል፡፡ እርግጥ ነው ከታሪክ መማር ታሪካዊ ስህተቶችን ላለመድግም እንደመሆኑ፤የመሪዎቻችንን ችግር በቢሆን ትንተና አጅቦ ማስቀመጡ እንዲማር የሚፈለገው ህዝቡ ነው ወይስ መሪዎቻችን የሚል ጥያቄ ያጭራል፡፡ ምክንያቱም መንግስቱ ሃይለማሪያም የንጉሱ መጨረሻ አይተው ጉልበት እንደሚከዳ ሲማሩ አላየንም፡፡ አብይ አህመድም ከመንግስቱ ሃይለማሪያም ውድቀት ከመማር ይልቅ እንደሳቸው ‘አስርዎቻችሁን ገድዬ መቶዎቻችሁን ዝም ማስባል እችላለሁ’ ብለው ሲደነፉ ነው የምንስማቸው፡፡ በአጭሩ ሲጠቀለል የአመራር ድክመት እውነት ነው አሰከፍሎናል፡፡እናስ? ምን
እናድርግ? የዚህ ትንተና ክፍል ተማሪ እኛ ህዝቦች ነንና እንዴት እንዚህን መሪዎች አነገስናቸው፤በአምባችንም አገነንናቸው በሚል መጠይቅ ብንቀጥል ወደ አቶ ልደቱ ሁለተኛ ትንተና ይመራናል፡፡
2.1.2.ፅንፈኝነት እና ጦረኛነት ማህበረሳባዊ አንኳር ችግራችን ነው
የፅንፈኝነት እና ጦረኛነት መንፈስ የምክንያት ትንተና ውስጥ እንደ ማህበረሰብ በወል ያሉብንን ችግሮች ልደቱ በሁለተኝነት ጠቀስ አድርገውታል፡፡ ጉዳይ ተስፋፈቶ ልንወያይበት የሚገባ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የአቶ ልደቱ የዚህኛው የግምገማ ክፍል ተጠቅመው የሀገሪቱን ህዝቦች በወል ያሉብንን ችግሮች ለመዳሰስ ባትሪ ያበሩበትን አቅጣጫ የማደንቀው እንደ ህዝብ ችግሮቻችንን ያለማውራት ችግር ስላለብን ነው፡፡ይህ እውነት ሆኖ ሳለ፤እውን የፅንፈኝነት እና ጦረኛነት መንፈስ የሚሉት ቃላት የገላጭነታቸው ደረጃ በላቀ ሁኔታ የሚታዩ ናቸው ወይ ብለን ትንሽ እናዝግም፡፡ ፅንፈኝነት የሚለው ተዘውታሪ የፖለቲካ ቃል ትረጉሙ በመግቢያው ላይ በተገለፅው አግባብ ሲሆን አከሳሰቱን ስናስተውል ደግሞ በሁሉም ህብረተሰብ ወስጥ ሊገኝ የሚችል በጥቂቶች ብቻ የሚቀነቀን ሃሳብ ነው ወደሚል እውነት ያመራናል ፡፡ በራሱ መጥፎም ጥሩም ነገር አይደለም፡፡ በአቶ ልደቱ ፅሁፍ ላይ አቀማመጡ አሻሚ ቢመስልም በተለምዶ ፅንፈኝነት የሚለውን ገላጭ የምንጠቀመው እርስ በእርሰ ለመወነጃጀል እና የማንወደውን ሃሳብ ወደዳር
ለማስወጣት ነው፡፡ ፀሀፊው እዚጋ በዚህ የመፈራረጅ መንፈስ ባይጽፉትም የበዛው አንባቢ በቀኝም ሆነ በግራ ጠርዘኞች ናቸው ተብለው የሚገመቱትን የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች በዓይነ-ህሊናው መሳሉ አይቀርም፡፡ ይህም ሳይናገሩ የማግባባት ያክል ጠንካራ መልዕክት(subliminal message) የማስተላለፍ ያክል ነው፡፡
ለምሳሌ ኢትዮጵያ የምትባል የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ፕሮጀክት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ላለ ህዝብ አዋጭ ስላልሆነ በሰላማዊ መንገድ ከዚህ ህብረት ፍቺ ማድረግ ያስፈልጋል የሚል የፖለቲካ አስተሳሰብ እንደ ፅንፈኝነት ብዙ ጊዜ ተፈርጆ ሲተነተን ይታያል፡፡ ሲጀምር ሃሰቡ የጥቂቶች መሆኑን ሳይረጋገጥ ዋልታ-ረገጥ ሊባል አይገባውም፡፡ ሲቀጥል ዋልታ-ረገጥነት የሃሳብ ገበያው የሚቀጣው ለሽያጭ የቀረበ አማራጭ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡ በዚህ እርቀት የአቶ ልደቱን ትንተና የምተችብት ምክንያት ዘውዳዊ ስርዓት እንዲመለስ የሚፈልጉ ስብስቦች በማህበረሰባችን ውስጥ መኖራቸው እንደ ችግር እንዲቆጠር በሁለት መነሻዎች
ትክክል ነው ብዬ ስለማላምን ነው፡፡አንድም የትም ያለ የማህበረሰብ ገጽታ ነው፤ ሁለትም በመፈራረጅ ጉልበታችን ዝሎ ሌሎች አንኳር ችግሮቻችንን እንዳናይ ስለሚጋርደን ነው፡፡
አሁን ደሞ ሌላውን አቶ ልደቱ የጦረኛነት መንፈስ በማለት የገለፁትን ሃሳብ ወደመመርምር እንሻጋገር፡፡ የሃገሪቱ የቅርብም ሆነ የሩቅ ታሪክ እንደሚያሳየን ያለ ጦርነት የቆይንባቸው ጊዚያት የሉም ቢባል ይቀላል፡፡ በአንደ በኩል ሲታይ ልዩነቶች ሲኖሩ
የሚፈቱበት ብቸኛው መንገድ ብረት ማንሳት እንደባህል የሚቆጠርበት ህብረተሰብ እንደሆንን ብዙ የሚጠቁመው ነገር አለ፡፡ የቅርቡን ቅድመ-ትግራይ ጦርነት ወቅት የህዝቡን አስተያየት ዞር ብለን ብንገመግመው በሚደንቅ ሁኔታ የብልጽግና አገዛዝ በትግራይ ክልል ላይ ለመውሰድ ባቆበቆበው ወታደራዊ እርምጃ ተገቢነት ላይ ብዙ ክርክር አይሰማም ነበር፡፡ ያ ሁሉ ውድመት ለመዝነብ ያዳመነበትን የክፍለዘመኑ ትልቅ የጦርነት ዋዜማ ላይ ሆነን ‘በለው በለው’ ያልንበት ሁኔታ በጦረኛነት መንፈስ ሆነን ነው ወይስ እንደ ማህበረሰብ ሌላም ጠንከር ያለ የወል ችግር ስላለብን? መልሱ ፊትለፊት ያለው አይመስለኝም፡፡ እንደ አቶ ልደቱ አገላለጽ ቢሆን ኖሮ በአሁኑ ሰዓት አገዛዙ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች ላይ እየፈጸመው ካለው አፋኝነትና ጦረኝነት አንፃር በብረት የሚያናግሩት በግምት ከ1 ከመቶ በታች የሆነው የህብረተሰብ ክፍል ብቻ አይሆኑም ነበር፡፡ በውጪ ‘በርገር እየበላ ያጫርሳል’
እየተባለ በተለምዶ የሚከሰሰው ዲያሰፖራ እንኳን ነገ ፋኖ ባህርዳርን ኦነሰ(OLA) የፊንፊኔን ዙሪያ ተቆጣጥሯል ቢባል በአውሮፓና የሰሜን አሜሪካ ከተሞች የሚፎክረውን ያክል ዛሬ ላይ በገንዘብ መዋጮ የትጥቀ ትግሉን የሚደግፍ አይደለም፡፡ እዚህ ጋር እንዲሰመርበት የምፈልገው ነጥብ አቶ ልደቱ በጽናት የኖሩበትም ሆነ በብዙ የሚሰብኩት የሰላማዊ ትግሉ ሜዳ ሰው የጠፋው በጦረኛነት መንፈስ ሁሉም ዝግር ነቅናቂ ሆኖ ሳይሆን፤ጉዳዩ ሌላ የማሃበረሰባችንን የወል ችግር ላይ የሚያመለክት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ታዲያ ታሪክን በሚቀይር መልኩ በጦሩም ሜዳ ሆነ አቶ ልደቱም ያዋጣል ብለው እፅንተው በሚነግሩን የሰላማዊ ትግል ሜዳ የሌለነው የት ሆነን ነው?
ሕዝብ የሚገባውን መሪ ያገኛል እንደሚባለው በአመራር ድክመት የምንወቅሳቸው መሪዎች የራሳችን ነጸብረቅ፤በሞራልም ሆነ አስተዋይነት ጠባያቸው የወጡበት ህዝብ ፍንካች ናቸው፡፡ ከቅርባችን ብንጀምር፤ አብይ አህመድ ኢህአዲግ ውስጥ ቤቱን በሰራ አደግድጎ በማደግ የባህል ጡብ የተሰሩ የህዝብ ውጤት ናቸው፡፡ ሰውየው በሚገባ ሳናውቃቸው የሽቃበጥንላቸው የግልብነታችን መገለጫ የኛው ስብራት ናቸው፡፡ እንደማህበረሰብ ስልጣንን ለመግራት ያለመቻላችን መገለጫ ድክመታችን ናቸው፡፡ ዛሬም ቢሆን በሌላ አፈ ጮሌ የማንጭበረበር ማህበረሰብ ነን ወይ? ብልን ብንጠይቅ መልሱ ከታሪክ እንደ ህዝብ ተምረናል ወይ የሚለው ላይ ያርፋል፡፡ ዲሞክራሲን ለአመታት የጮህንለት ነገር ቢሆንም በእርስ በእርስ ግንኙነታችን እንኳን የግለሰብን ነጻነት ለማክበር ‘እንደፍጥርጥሩ’ ለማለት የሚከብደን ህዝቦች ነን፡፡ በመጨረሻዎቹ የደርግ ያገዛዝ ወራት አካባቢ ‘መንግስቱ ሃይለማርያምን ለማናገር እንፈልጋልን’ ብሎ ጠይቆ ሲበቃ፤ በአካል ሲገኙም ለመሞገት ይጠበቅ የነበረ ወፈሰማይ የአዲስ አበባ ዩንቨርሰቲ ተማሪ ፕሬዘደንቱ ትዘምታላችሁ ወይስ አትዘምቱም? ብሎ ሲጠይቅ አስማት እንደተሰራበት እደለቢስ አዎ ብለን ጦላይ የተላክነው እኛው ነን፡፡
ብዙ ዓመታትም አልፈው አሁን በዚህ ጊዜ ባሉት ጠቅላይ ሚኒስተሩ ሲሰደብ የሚስቅ፤ሊያነሳቸው በሚችል አንድ ተወካይ በጅምላ ሲጣጣል የማይሰማው የተወካዮች ምክርቤትም የወጣው ከእኛው ውስጥ ነው፡፡ ኣቶ ልደቱ በትክክል እንዳነሱት ምንም እንኳን
ጦረኝነት እንደ ማህበሰብ የወል በሽታችን አይደለም ባልልም (በብዙ ሆይታ የትግራይ ጦርነት ሲከፈት የዘፈነውን ህዝብ ብዛት እንዴት ልረሳ እችላለሁ!?) ዓይን ለዓይን እየተያየን ከተነጋገርን ዋነኛ ችግራችን ከሰላማዊ ትግል ይልቅ በጦርነት ማመናችን አይመስለኝም፡፡ ትርጉም ያለው ለውጥ በሚያመጣ መልኩ እንዳንታገል ከነፍጡም ከመፈክሩም የለንበትም፡፡ ዋነኛ ችግራችን በመንጋነት ራሳችንንም ሆነ ሌላውን ነፃነት መንፍግ እና በአድርባይነት ከራስ ጥቅም በሚያጻርር ጎዳና መንጎድ ናቸው፡፡ ይሄን ሁሉ ወቀሳ ህዝብ ላይ አንድ ፖለቲከኛ እንዲያዘንብ ባልጠብቅም እሰካሁን ለገባንበት ቀንበር፤ ወደፊትም ለምንገባበትም ጉድጓድ
ቆፋሪዎቹ እኛው መሆናችንን ማወቅ በጊዜ እንደዜጎች እራሳችን ላይ መስራት ያለብንን ስራ ግልጽ ያደርግልናል፡፡ ያሁኑን አምባገነንም ለማስወገድ ቀጣዩንም ለማስቆም እንዚህን የወል ድክመቶቻችንን ማከም አለብን፡፡ አሁን ላለንብት ምስቅልቅል የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ የምንላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዛሬ ከአራት ኪሎ ብን ብለው ቢጠፉ እንኳን የለውጥ ተስፋውን የሚመራ ፖለቲካ ስብስብ ብቻ ሳይሆን የሚሸከምም ህዝብ መፍጠር ካልቻልን ተመልሶ እንቦጭ መሆኑ አይቀርም፡፡
2.1.3.የብሔርተኝነት ፖለቲካ በአቶ ልደቱ እይታ
ችግሮቹን የገለጹበት ቅደም ተከተል ክብደታቸውን ይገልጻል ተብሎ ባይገመትም በመጨረሻ ላይ አቶ ልደቱ ያነሱት ጉዳይ የብሔርተኝነት ፖለቲካ ነው፡፡ የተሰጠውም የትንተና ስፋት ካየነው ከፊተኞቹ ሁለቱ ላቅ ያለ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ምናልባትም ሀገሪቱን የበጠበጡት በዐብይ ብሄር እና ንዑስ ብሔር ርዕዮት ስር የተቧደኑ ሃይሎች ናቸው ብለው ከመደምደምና ሁለቱንም ላይ የሰላ ትችት በማቅረብ አቶ ልደቱ የመሃክለኛውን አስታራቂ መንገድ በመከተል ተዓማኒነትን ለመፍጠርና መቀራረብን ለማጎልበት ያደረጉት ነው ተብሎም ሊታሰብ ይችላል፡፡
ይህ ሃሳብ በራሱ መጥፎ አይደለም ብቻ ተብሎ የሚገለጽ ሳይሆን ሌሎችም ሊሞክሩት የሚገባ መልካም ተግባር
ነው፡፡ ነገር ግን የአቶ ልደቱ ማሃከለኝነት ከቀኝ የሚነሳ መሆኑን፤በዚህም ምክንያት ‘እንተም ተው! አንቺም ተይ!’ ቢሉም ለብሄርተኝነትን ርዮት ያላቸውን ቀና አተያይ በሚያሳጣ መልኩ በአንድ መስመር ‘ይህ ማለት ግን ብሔርተኝነት የራሱ የሆነ ጠንካራ ጎን የለውም ማለት አይደለም።’ በማለት እንዲያዳፍኑት አድርጎቸዋል፡፡
አቶ ልደቱ የብሔርተኝነት ፖለቲካን ብዙ ጊዜ እንደሚደመጠው የጎሳ ፖለቲካ ወይም ዘውጌ ባለማለታቸው ከዚህም ባለፈ ‘በህግ ይታገድለን፤ከፖለቲካ መዝገበ ቃላታችንም ይፋቅልን’ ስላላሉ ይመሰገናሉ፡፡ ለቋንቋ እና ባህል መከበር የሚያሳዩትን ቁርጠኝነት በዚህም ጽሁፍ ውስጥ ብዙ ቦታ እንደመጥቀሳቸው ምናልባትም የብዝሃ-ባህል ሀገረ መንግስት (multicultural nation state)
እንደሚስማማቸው ነገር ግን የብዝሃብሄር ፈደሪሽንን (multinational ethnic federation) መዋቅራዊ ገዢ አስተሳሰብን ያዋለደ ነው ብለው ሰለሚስቡ አምርረው በሃይለቃል መወገድ አለበት ይላሉ፡፡
መዋቅራዊ ገዢ አስተሳሰብን ሽሮ ሊመጣ የሚገባውን አከላለል ለውይይት በሚበቃ መልኩ በምሳሌ ቢያስደግፉት ለሃሳብ ልውውጥ የሚስብ ይሆን ነበር፡፡ እሳቸው ባላብራሩት ጉዳይ ላይ ብዙ አስተያየት መስጠት ተገቢ ባይሆንም የተወሰኑ ጥያቄዎችን መጠየቅ ግን ወደፊት ሊደረግ በሚችለው ውይይት ላይ ጥቂት ብርሃን ሊፈነጥቅ ይችላል፡፡
ሀ. የብሔርተኝነት ፖለቲካ መዋቅራዊ ገዢ አስተሳሰብ ብለው የገለጹት አሁን ያለውን የክልሎች ስያሜ፤ይዞታና የክልል ህገመንግስታዊ ብያኔአቸውን ነው ወይስ ሌላ?
ለ. ከሆነም እዚህ ውስጥ ‘ይሄኛው ክልል የሸንሸንልን ይሁኛው ደግሞ ይከለስልን ሌላኛው ደሞ ይጥፋልን’ የሚል ግብታዊ የቀኝ ዘመሙን ጥያቄ በጨዋ ቋንቋ ያቀረበ ጥያቄ ነው ወይ?
ሐ. ያቀረቡት በህገ-መንግስታው ማሻሻያ ሆነ የፊደራል ስርዓቱን በአዲስ ክልላዊ ቅርጽ የማዋቀር ሃሳብ በዲሞክራሲያዊ አካሔድ በህዝቦች ይሁንታ መፈጸም እንዳለበት እንደሚያምኑ ባልጠራጠርም፤ሊብን ወረዳን ከቦርና ቀላቅለው ቦረናን ከቀሌም ወለጋ በመለያየት ማን ምን እና እንዴት እንደሚጠቀም ቢያስረዱ መልካም ይሆናል፡፡
መ. ክልሎች ፈርሰው እንደአዲስ ሲዋቀሩ ከፌደራል ምንግሰቱ ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት ይኖራቸዋል? ክልላዊ ቋንቋ እና ህገመንግስት የሚኖራቸው ይመስሎታል?
ረ. በመጨረሻም ብሔርተኞች መዋቅራዊ ገዢ አስተሳሰብ የተባለው ቢወገድ ምን ይጎልብናል ብለው እንደሚያስቡ መገመት ይችላሉ?
2.2. የፀሃፊው ሃይል አሰላለፍ ትንተና
2.2.1. የሃይል አሰላለፉ ትንተና ቅርጽና ተሸጋጋሪ ገጽታዎች
ፀሃፊው አሁን ባለው የፖለቲካ መድረክ ላይ በወሳኝ ተዋናይነት ሚና ኣላቸው ያሉትን አካላት ሲዘረዝሩ የብልጽግና ፓርቲ(1)፤የኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች(2) ፤ የትግራይ የፖለቲካ ኃይሎች(3)፤ የአማራ የፖለቲካ ኃይሎች(4)፤ አገራዊ የፖለቲካ ኃይሎች(5) እና በመጨረሻም ፤“ዳያስፖራው” (6) ናቸው በማለት ይጠቀልላሉ፡፡ እውነት ነው እዚህ የተጠቀሱት ተዋንያን ላይ
ተመስርተን አስተዋጽኦቸውን መገምገምና የመፍተሄው አካል ለመሆን ማስተካከል ያለባቸውን ጉድለቶች መንቀሱም መልካም ነው፡፡ ነገር ግን በተለመደው የፖለቲካ ተወስኦችን(Political discorse)ና መዝገበ ቃላታችን(political lexicon) ተጠቅመን ልየታውን ከጀመርን አንድም የምንሳሳተው፤ሁለትም ተረስቶ የምንዘለው አካል ኖሮ የትንታኔችን ምልኡነትን(comprehenisvness) ይጎዳዋል፡፡
ይህንን ሃሳብ እስቲ በምሳሌ እንየው ካልን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደ አንድ የራሱ ባህሪ፤ፍላጎት እና ዓላማ እንዳለው አካል ሊተነተኑ የሚገባቸው ተዋናይ ናቸው፡፡ ከፓርቴያቸው ጋር አጃምሎ መተንተኑ ወደ መፍትሄው ሲኬድ ክፍተት ሊፈርጥ ይችላል፡፡ሌላው በአቶ ልደቱ ተረሱ ከሚባሉ መሃል በብዙ ሃገሮችም ሆነ በእኛም ሀገር እንደታየው ወታደሩ በእንቅስቃሴውም ሆነ በዝምተው
ከወሳኛ ተዋናይነት አውጥተን ልናየው አንችልም፡፡ እዚህ ጋር የሚነሳው ክርክር የተዋናይነት መስፈርቱ አሁናዊ አቅማምነቱ (current potency) ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ወቅት ጨዋታ ቀያሪ(game changer) እምቅ ሃይል ያለው መሆኑ ነው፡፡ ባልተንዛዛም መልኩ በሃገሪቱ ውስጥ ያሉትን ተቋማት (በተለይ የፍትህ እና የጸጥታ) ትተናው ውስጥ ማስገባቱም ሊጤን የሚገባው ነገር ነው፡፡
ሌላው በሃይል ትንታነው ክፍል ቢታይ መልካም ሊሆን የሚችለው ጉዳይ አንዳንድ ተዋንያንን አጃምሎ ማለፉ ነው፡፡ ቢፍታቱ እና ቢዳቀሉ ብዙ ትምህርት ልናገኝባቸውን የምንችላቸውን የተዋንያኑን ጥሩም ሆነ ደካማ ጎን ሳይዳሰስ በማለፉ ነው፡፡ ለምሳሌ ዳያስፖራው ተብሎ የተገለፀው በብሄር ስብጥሩ ድረጊቶቹ ቢተነተኑ የተሻለ ብርሃን ለወደፊቱ ይፈነጥቃል፡፡ የጀመርነውን ማሳያ በበለጠ ሲብራራ፤ የትግራይን ዲያሰፖራ ከአማሃራ ዲሰፖራ እያስተያየን የተጫወቱትን ሚና (በጎም ሆነ መጥፎ) ብንገመግም በሚቀጥለው የመፍትሄ ምዕራፍ ሊባል የሚችል ጠቃሚ ነገር ሊወጣው ይችላል፡፡ ታናንትም ዛሬም በብዙ ጭፍጨፋ እየተካፈሉ ያሉ የጦሩ መሪዎች በዓለም ላይ በሰላም እየዞሩ ያሉት ምናልባትም የተቀረው ዲያሰፖራ እንደ ትግራይ ዲያሰፖራ ጫና ለማሳደር መስራት ላይ ልግመኛነት ሰለሚታይበት ይሆናል፡፡ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁን ዓለም አቀፍ ውግዘት የደረሰባቸው የገደሉት ፍልስጤማዊ ቁጥር የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ካጨደው የሚያንስ ሆኖ ነው ፊልድ ማርሻሉ ከሮም እሰከ አንካራ ሽር ብትን የሚሉት?
የአሰላለፍ የሃይል ትንተናው የውስጥና የውጪ ተብሎ ተከፈሎ ለየብቻም ቢሆን ቢታይ ተገቢ ነው፡፡ አሁንም የትንተናው ግብ ለመፍትሄው መንደርደሪያ ለማመቻቻት እስከሆነ ድረስ የምዕራባዊያንን ተጽዕኖ እንዴት መዘንጋት ይቻላል? እንደ ኤርትራ እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስን ጣልቃ-ገብነት፤መሪዎቻችንንም እስከ መቆጣጠር የደረሰ ጉልበታቸውን እንዴት ወደጎን ልንለው እንችላለን? ነገሩ ውስብስብ መሆኑን እረዳለሁ፡፡ ነገር ግን ራሰችንን በሆሜር ታሪክ ውሰጥ እንደተሳለው ኦዲሲስ ጀግና ተጓዥ ብንስለው በመንገዳችን ብዙ ፈተና ከተለያየ ተገዳዳሪ አስፈሪ አውሬዎች ያጋጥሙናል፡፡ ወደ ትሰፋዬቱ ምድር የምናደርገው የጉዞችንን ዘመን በዓመታት ሊያራዝሙ የሚችሉ አደናቃፊ ጠላቶቻችንን፤የሚያጋጥሙንን ዘንዶዎች እያሰላን መጓዝ ምርጫ አይደለም-ግዴታ ነው! የኢትዮጵውያንን ብሄራዊ ጥቅም ብቻ ላይ ተመስርቶ የሌሎችን ብሄራዊ ጥቅም የማይጎዳ ሀገራዊ ንቅናቄ እውን መሆን ቢችል፤ንቅናቄው በአንድ ድምጽ ለወታደሩና አዛዦቹ ጥሪ ማስተላለፍ አለበት፡፡ ከጥቂቶች ተሻርኮ ሀገሪቷን የአዳዲስ ጦር መሣሪያ መለማመጃ፤ የአምባገነኖች መፈንጫ እንድትሆን ተግቶ የሚሰራ ጣልቃገብ የውጪ መንግስት በስሙ ተጠርቶ በንቀናቄው አካል እጅህን ሰብስብ ሊባል ግድ ነው፡፡ አጋዥ ሊሆኑ የሚችሉ ሀገራትንም በተዋናይነት ሚናቸው ጉልህ እና አወንታዊ ሆኖ ሲገኝ ማቀረብም ማስረዳትም ተገቢ ነው፡፡
እነዚህን ሁሉ ለትግሉ አወንታዊም ሆነ አሉታዊ ያላቸውን፤አሰላለፋቸው ከውስጥም ሆነ ከውጪ የሚነሱ ሃይሎችን ልየታ ላይ ከውስብስብነቱ የተነሳ ሙሉ ለሙሉ መግባባት አይቻል ይሆናል፡፡ ነገር ግን በጠንካራ አመክንዮ ላይ የተመሰረተ የጋራ ልየታ ሞደል እና ሂደት ግን የግድ ነው፡፡
ለዚህ ጽሁፍ መነሻ በማዘጋጀት ወቅት የራሴን የተሟላ ምስል እና ሁሉን-ዓቀፍ የህዝብ፤የልሂቃን እና የስልጣን ኮሪደር ተናጣቂዎችን ሞዴል ለመፍጠር ስሞክር የተረዳሁትም ከዚህ በታች የሚታውን ዓይነት ውስብስብ መስተጋብር ነው፡፡
ምድብ 1
በዚህ ሞዴል ሶስቱ ዋነኛ አካላት ተብለው የተለዩት
የሚጋለበው ፈረስ(1)፤
ገሪዎቹ(2) እና
ጋላቢው ወይም የፈረሱ ባለቤት(3) ናቸው፡፡
በምድብ አንድ ያሉት ሁሉም ለቀጥተኛ የስልጣን ወንበር በህዝብ ይሁንታ በተገኘም ሆነ በተሰረቀ ድምጽ፤ተወዳድረው ባገኙትና በሚቆጣጠሩት የፓርላማ ወንበር ይሁን በነፍጥ ነጥቀው በያዙት ነጻ ወረዳ ላይ ነገሮችን ለመከወን እድል ያላቸው አካላት ናቸው፡፡ መገራት ያለባቸውም ወድያውኑ ሊዘረዘር የሚችል የመከወን ጉልብት በእጃቸው ስላለ ነው፡፡ በሁለተኛው ምድብ ያሉቱ ደሞ ተደማጭነትን በምሁራዊ ብቃት፤ በኢኮኖሚዊ ጡንቻ፤ በባሀላዊ እነ ኪነጥበባዊ አበርክቶዎቻቸው ልቀት፤ ተሰሚነታቸው የገዘፉ ሰብዕናዎችን ነው፡፡ ዲያሰፖራ መሆንም በነፃ ሀብታም ሃገር ላይ ከመኖር ጋራ ተያይዞ ከሰፊው ህዝብ በንፅፅር በተሻለ ለመሰማት ተጽዕኖም ለማሳደር መነሻ ሰለሚሆን ከዚሁ ምድብ ቢቀመጡ ተገቢ ይሆናል፡፡ ከሳተላይት ቴሌቪዥን እሰከ ብዙ ተከታይ ያለው የማህበራዊ ሚዲያ አክቲቪሰቶችም እዚሁ ውስጥ የሚጠቃለሉ ናቸው፡፡ ሶስተኛው ምደብ በተለምዶው ህዝቡ የምንለው ብዙሃኑ ነው፡፡ ፍላጎቶቹ ድብቅ ባይሆኑም በተራቀቀ ብልጠት የሚድበሰበስበት፤በእናወቅልሃለን የሚቃለልበት ሰፊው ህዘብ አድራሻው እዚህ ነው፡፡
በምድብ 2 ላይ ባሉት ከአብራኩ በወጡት ልሂቃን ልጆቹ ከተንቀሳቀሰ እንደ ፓሪስ ኮሜውን የፈረንሳይ አብዮት የገዢዎችን አንገት የሚቆርጥ ሰይፍ አለው፡፡ በአሁኑ ወቅት እንዳለው የምዕራቡ ዓለም ሰፊው ህዝብ መብቱን የሚያውቅና በአንጻራዊነት የነቃ ብዙሃን ከሆነ ደግሞ በተገራ ፈረስ ሰረገላውን የሚቆጣጠር እድለኛ ተጓዥ ነው፡፡ ይህን ያህል ስለ ተዋንያኑ መስተጋብር እና ዝርዝር ካወጋን ከንደፈ-ሃሳባዊው ጉዳይ ወጥተን ራሳችንን የሚመለከት ጥያቄዎች እንጠይቅ፡፡
ለአንድ ህዝብ ልሂቅ መሆን ጥቂቶች ብቻ በሚረዱት መልኩ ሸክም ነው፡፡ ታላቅ ወንድም መሆን ‘የወንድሜ ጠባቂ እኔ ነኝ!’ በሚያስብል ደረጃ ሃላፊነቱ ግልጽ ነው፡፡ አልያ ወንድምነት አልቦ፤ ብኩርናም ከንቱ ነው! በተለምዶ ‘ሳይማር ያስተማረንን’ ብለን የምንገልጸውን ህብረተሰብ እኛ የምሁራን ሊሂቆቹ ‘መሪ ተገኝቶ ህዝብ ጠፋ’ ብለን መግራት ላለብን ስብስብ ማደግደጋችን አሳፈሪ
ነው፡፡ ጥቂቶች የማንባል ጉልበትን በዕውቀት የመግራት ሃላፊነታችንን ረስተን ግብር ይጣላል በተባለበት ቦታ ሁሉ አቁማዳችንን ይዘን ቆመናል፡፡ የቀረነው ደሞ በግለሰብ ደረጃ እንኳን እውነት ከአፋችን እንዳትወጣ አለቅጥ በሰፈረብን ፍርሃት የተነሳ ቀብረናታል፡፡ የማይሸጥ የለም ላለ አምባገነን በጧቱ ‘በኪስህ አኑረኝ!’ ብለን ብኩርናችንን ሸጠናል፡፡ የሃይማኖት ፊተኞቻችንስ ተናግረው ሰላምን ነው ወይስ መጋደልን ያበዙልን? በዝምታቸው የደነቆረ ጆራችን ለወደፊት ድምጻቸው ተምቡሩ ይሰራ ይሆን? ከሁሉም ብሔር ስማቸውን ልናነሳ የምንችላቸው ድምፃዎቻችን፤ገጣሚዎቻችን፤በአጠቃላይ የኪነጥበብ ባለሙያዎቻችን ፈረሱን ለመግራት ምን ኣይነት ሚና ሲጫወቱ ነበረ? ስንቶቹ አፈር ሆኑ፤በረሃ ወረዱ ወይስ ለአገዛዙ ዋሽንት በስልት እየደነሱ ጭፍጨፋን አፋፋሙ?
የኢኮኖሚው ኢሊቶቻችን እኛው መሃል ነግደው ለመጣው እና ለሔደው እያጎበደዱ በመስተጋብሩ ውስጥ ያለውን ግዴታቸውን እንዴት በዘዴ በሻሽ ቀበሩት? ለነጻነት ትግላችን ሣይገብሩ እንዴትስ በላባችን ወዝ ወዙ? ወይስ በመንግስት በሚዘወር ኢኮኖሚ ከጥቂት ጥገኛ ባለሀብት ውጪ ሰላላፈራን በሀገሩ የሉም ይሆንን? ከዚህ ጎስቋላ ህዝብ ላይ የኢኮኖሚ ኢሊት ለመሆን በስንት
ጥማድ ማረስስ መመዘኛ ይሆን? አላውቅም፤ውይይት ያስፈልገዋል፡፡ ሀገሪቱ ለህዝቦቿ ገነት ሆና ባታውቅም፤ እንደ ባለፉት 6 ዓመታት ግን ሲኦል ሆና ነበር ማለት ለእውነት በጣም የቀረበ አባባል ነው፡፡ ሲኦል እንድትሆን ሁላችንም ችቦ ለኩሰናል ማለት ግን
የአገዛዙን ቁንጮዎች ነጻ እንደማውጣት ካልተቆጠረ የሆነውን ሁሉ ለማስቆም የሚያስችል ሁሉን-ዓቀፍ የኢሊቶች አወንታዊ አበርክቶት ጠፍቶ እንደነበር በጉልህ ዛሬ ላይ ቆመን ማስመር አለብን እንጂ የተለመዱትን የየብሔሩ ብርተኞችን፤ የብሄር ልሂቃንን እና ውስን የፖለቲካ ፓርቲዎችን በመሄስ የምንማረውም ትምህርት፤ ትምህርቱንም ተጠቅመን የምናድነው ሀገር
መኖሩ እጠራጠራለሁ፡፡
አቶ ልደቱ አንድ ነገር የመሆን ዕድሉን በነፃ መንፈስ ከመቶኛ እያሰሉ ብዙ ጊዜ ያስቀምጣሉ፡፡ የምንነጋገረው የዕውቀት ክልል ጠጣር ሳይንስ (Hard Science) ከሚባሉት የሚመደብ ስላልሆነና በማህበራዊ ሳይንስ ዘርፍ በሀገራችን መረጃን ፈትለን እንዳንሸምነው የመረጃው ጥሬ እቃ፤ የሸማኔ ብልሃቱም ዕቃውም ሰለሌለን ብዙም መቶኛቸውን ዓይናችንን ቡዝዝ አረገን ከመመዘን ባለፈ የሚተችበት ጎን የለውም፡፡ በዚሁ የነፃነት መንፈስ መቶኛዎችን ተጠቀመን ማን ምን አዋጣ ብንልና የአጭር ጊዜ ቀጣይ ተወንያንን እንዴት ማውጣት እንችላለን? ይሄ ሥራ ብዙ ሰዎችን የሚያሳትፍ መጠይቅ ተበትኖ ቃለመጠይቅ ተተንትኖ የሚገኝ ነገር ቢሆንም በምድብ ዘርዝረን ያስቀመጥናቸውን አካላት ለየብቻ የተሳትፎ ድመቀታቸውን ብንመረምር በተወሰነ የጠራ ምስል ማግኘት እንችላለን፡፡
ከተወሰነ በከተሞች እዚህም እዛ ከነበረ ረብሻ እና ሁከት ውጪ ቅድመ 2010 ኢትዮጵያ ከመጀመሪያዎቹ ድህር 2010 ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ከመቀየር ውጪ ብዙም የተለየች አልነበረችም፡፡ ከዛ በኃላ የተፋፋመው ፖለቲካዊ ግድያዎች፤የዲሞክራሲያዊ ሂደት መሸራረፎ እና የለየለት ክፍለ ዘመናችን ጦርነት በኃለማርያም ደስአለኝ ጊዜ ሊከሰት ይችል ነበር ብለን እንጠይቅ? በብዙ የሀገር ዕልቂት መሃል የተማርነው ነገር ቢኖር የአብይ አህመድን ሚና ቁልፍ ነው፡፡ እንዲህ እየጠየቅን ብንዘልቅ ሀገሪቷን ባለፉት 6 ዓመታት ወደሲኦልነት የቀየሯት ተዋናዮች ድርሻ ከመቶኛው ሲሰላ የሚከተለውን ይመስላል በግምት እላለሁ፡፡
ደግሞ በመግቢያው ላይ የተነሳውን ለማስታወስ ያክል ትንተና 1፤2፤እና 3 ብለን ከጠቀስናቸው መሃል ዛሬ የሲዖል ደጃፍ ላይ ቆመን የምናደርገው ግመገማ በቁጥር 1 ላይ ያስቀመጥነውን መሆን ያለበት፡፡ ሚሊዮን ለሞት፤ሌላ ሚሊዮን ለአካል እና ስነልቦናዊ ቀውስ፤ብዙ ሚሊየኖችን ለመፈናቀል፤ለቢሊዮን ዶላሮች የሀገር ኢኮኖሚ ኪሳራ ለምን ለምን ተዳረግን? የትንተናችን መደምደሚያ አብይ አህመድን፤ አምባገነንነታዊነታቸውን ያዋለደው ብልጽግናን እና የውጪ ሃይሎች ለብቻቸው ሀገራችንን ወደሲኦል ደጃፍ ላደረግችው የአንድ መንገድ ጉዞ ያደረጉትን አስተዋፅዖ ግልጽ ሆኖ ካላሳየን አሁንም ከጫካው አልወጣንም፡፡ ሌላው የምሁራዊው ለሂቅ እንበለው የባህላዊው አበርክቶቱ ሲደመር ዙፈን ላይ ያሉትን ያክላልም ብለን ልንስማም እንችላለን እንጂ ከተለመዶአዊው የፖለቲካ ጎራችን ውስጥ ተወዳጅ የሆነውን የምክንያትና ውጤት ግንኙነት በማምጣት ትንተናውን ማደፍረስ የለብንም ብዩ አስባለሁ፡፡ አባቴ ሲተርት እንደማስታውሰው ‘ጅረት አይበላም፤ነገር ግን ይዞ ለሚሔድ ወንዝ ያደርሳል’ ነው ጉዳዩ፡፡ ሲጠቀለል
o የቅርብ ጊዜ ሀገሪቱ የገባችበትን ጣጣ እና ለዚህም ችግር ከፍ ያለ አበርክትዎት ያላቸውን አካላት በምልሰት ተንትነን ዛሬ ላይ በአፀደ-ስጋ ያሉቱ እንዚሁ ተዋንያን በተመሳሳይ ዐቅም ውስጥ ሆነው በማደረግም(commission) ሆነ በዝምታ(omission) ጣጣው እንዲቀጥል የሚያደርጉ መሆናቸውን የምንስማማበት ነገር መሆኑ፤
o ከላይ ከተዘረዘሩት ተዋንያን ውስጥ በፖለቲካዊ አቋማቸው የማይጥመንን ነገር ግን ላለፈውም ሆነ ለሚቀጥለው አበሳ አብርክቶዎቻቸው በተነጻጻሪ አናሳ የሆኑትን አውቀንም ሆነ ሳናወቅ አግዝፈን በመሳል ምንም አወንታዊ ውጤት እንደማይገኝ፤
o የሃይል አሰላለፍ ትንተናችን የትኛውንም ተዋናይ ያለውን አሉታዊ አበርክቶት የማያዘነጋ፤የሌለውን የማይፈጥር እንዲሁም ትንሹን የማያገዝፍ፤ትልቁንም አቃሎ የማያይ እንዲሆን ከተለመዶዊው የፖለቲካ መዝገበ-ቃለት ( political lexicon cliché)
የዘለለ ሳይንስ-ቀመስ ዘዴ ቢኖረው
o ተዋንያኑ ከግለሰብ እስከ ሀገራት የዘለለ የቋሚነት ህልው (Permanence existaence /
አብ አህመድ ነገ በወታደራዊ ኩዴታ ሊወገዱ የሚችሉ ወይም በራሳቸው ተነሳሽነት ዛሬ ማታ በብሄራዊው
ቴሌቪዝን ቀርበው ‘ለእሰካሁኑ ሃላፊነት እወስዳለሁ፤ ስላጣኔንም ነገ አስረክባለሁ፡፡’ በማለት ድንገት ከሃይል አሰላለፉ
ሊወጡ የሚችሉ ናቸው፡፡ ነገረ ግን የሊሃቃኖቻችን ስልጣንን ያለመግራት ችግር ለመቅረፍ ብዙ ጊዜ የሚወስድ ነው፡፡) ጠባይ እንዳለቸው መረዳት፤ እንዲሁም ለለውጥም(የሚቀየሩ ከሆነ) ያላቸው ዕድል የአጭር እና የረጅም ጊዜ እንደሆነ (Transformation Evolution/ሀገራት ሉአላዊነታችንን እንዲያከብሩ ማሰገንዘብ ከሚያመጣው የመሻሻል ፍጥነት ይልቅ ሰፊው ህዝቡ የስልጣን
ባለቤትነት ምብቱን እንዲለማማድ ማደረግ ረጅም የለውጥ ሂደት ይፈልጋል፡፡) በመጨረሻም በግብታዊነት አቋማቸውን በመቀያየር ረግድም (Whimsical Goal Shiftting/በግለሰቦች በጎ ፍቃድ ላ የተመሰረተ በጎ ጅምርም ሆነ እርምጃ በአጭሩ ተቀልባሽ የመሆን እድሉ የጎላ ነው፡፡) እንደሚለያዩ መገንዘብ ጠቃሚነት እያሰመርኩበት፤ በመጨረሻ ደግሜ ማስታወስ የምፈልገው ነገር በአቶ ልደቱ የቀረቡልን የሃይል አሰላለፍ ቅርጽና ይዘት ትንተና እንደመነሻ ወስደን ትግሉን በሚደግፍ መልኩ በፖለቲካ ምሁራኖቻችን እንዲዳብር ጥሪ እያስተላለፍኩኝ ለትንተና ከመረጡት ተዋናይ መካከል አንዱን በመመረጥ ተጨማሪ የውይይት ማዳበሪያ ላክል፡፡
2.2.2. አቶ ልደቱ ከመረጡት የትንታኔ አንጓ አንዱን – የኦሮሞ ሃይሎች
የኦሮሞ ፖለቲካ ሃይሎች ተብለው የተገለፁት ምድብተኞች በአቶ ልደቱ አገላለጥ ብሔርተኛ ርዕዮታዊ አመለካከታቸው አንድ ስለሚያደርጋቸው በገዥውም ሆነ በተቃዋሚው ወገን መሰለፋቸው ለትንተናቸው ትርጉም ያለው ልዩነት የሚሰጥ ሆኖ ሲቆጠር አይታይም፡፡ ከዚያም አልፈው የ‘ባልበላውም ጭሬ ልበትነው’ ዓይነት የፖለቲካ በሽታ የወል ሰለባ አርገውም ይቆጥሯቸዋል፡፡ በዚህ ምሳሌያዊ አገላለጽ ፍቺ ‘መብላት’ ከመግዛት እንዲሁም ‘መበተን’ ሀገር ከማፍረስ ጋር አቻ ትርጉም እንደሰጧቸው በጊዜ ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡
አስተያየታቸው ብልጽግና ኢ-ህገመንግስታዊ የምርጫ ማራዘሚያ ባደረገበት ወቅት አካሄዱ ትክክል እንዳልሆነ እና የሽግግሩን ዲሞክረሲያዊ ሂደት ረብሾ ወደተለመደው አምባገነናዊ አረንቋ እንደሚከተን ለህዝቡ አበክረው በመግለጽ፤ጥርስ ያስነከሰባቸውን ትግል ከማን ጋር እንደጀመሩ የረሳ ይመስላል፡፡ በሃይል አሰላለፍ ረገድ አቶ ጀዋር የአቶ ልደቱ አጋር እንጂ የአብይ ረድፈኛ ነበሩ
እንደማለት ነው በግልጽ አማርኛ፡፡ ዘግናኝ የሆነው ጦርነት መነሻ ነጥብ ላይ ቆመን በነበርንብት ወቅት ራሱ ከመንግስት ውጪ የነበረው ብሔርተኛ ኦሮሞ የሲዖል ደጆች እንደይከፈቱ የጮህውን መርሳትም ትንታኔውን ያጎለዋል፡፡ እስቲ ከብልጽግና ፓርቲ አዳማቂዎች እና መሪው ውጪ መተላለቁን የደገፈ(እንደውም ያልተቃወመ) እና ራሱን በኦሮሞ ብሄርተኝነት የሚገለጽ ልሂቅ
ቢፈልጉ ያገኙ ይሆን? እንጃ! አንድ ስም ካመጡ ግን በተቃራኒው የሚቆም አቻ ምሳሌ 3 እጥፍ ማመጣት አይከብድም፡፡ በተለይ አገዛዙን የኦሮሞ እንደሆነ ተደርጎ እንዳይበየን የለፉበትን እንቀጾች ብልጽግና እና መሪውን እንደዋና የኦሮሞ ሃይሎች አድርጎ መሳል ይቃረነዋል፡፡ ይህ የኦሮሞን የፖለቲካ ሃይሎችን ለማጽደቅ የመጣ ክርክር ተደርጎ አይወሰድብኝ፡፡ የሚወቀሱበት ብዙ አበሳ አለባቸው ብዬ አምናለሁና በዚህ ፅሁፍ ውስጥ ወደፊት ነቅሼ የማወጣው ጉዳይ ነው፡፡ ለጊዜው ግን አቶ ልደቱ የኦሮሞ ሃይሎች የወል በሽታ ነው የሚሉት ጉዳይን መነሻ በዚህ መልክ ልከልሰውና አንድ ተጨማሪ ሃሳብ አንስቼ ላጠቃል፡፡
አብይ አህመድ እኔ ሀገረ መንግስቱን በፈለኩት መንገድ ካለገዛውት እበትነዋለሁ እያሉ የውጪ መንግስታትን ሁሉ እንደሚያሰፈራሩ እንሰማለን፡፡ በውስጥ የኦሮሞ ብልጽግና ፖለቲካዊ መድረኮችም ላይ ደግሞ ‘ሙሉ ድጋፍ ካለሰጣችሁኝ ኦሮሞን እንደይነሳ አድርጌ እሰብረዋለሁ!’ እያሉ በአደባባይ ሲናገሩ መሰማታቸው ምስጢር አይደለም፡፡ ታድያ የእኚህን ሰውዬ ግልጽ ያለ
የማሰፈራራት እና አደገኛ ቁማርተኝነት ጨዋታ ህግን (blackmailing, extortionist and brinkmanship) በጅምላ ለኦሮሞ የፖለቲካ ሃይሎች መሸለም ምን ፋይዳ ያመጣል? ለንጽጽር እንዲመች ከዚህ በታች በሠንጠረዥ የብዝሁኑን የኦሮሞ ብሄርተኞች አስተሳሰብ (thought pattern) ከአብይ ጋር አያይዤ ልደቱ የሁለቱን ልዩነት መጨፍለቃቸውን አስረድቼ ወደሌላው
ትችታቸው አልፋለሁ፡፡
አቶ ልደቱ በቀኝ ዘመሙ የፖለቲካ ተዋስዖ (rightwing political discourse) ውስጥ ጆሮ-ገብ የሆነውን የኦሮሞ ብሄርተኝነትን እወክለዋለሁ ከሚለው ማህበረሰብ መሰረታዊ ጥያቄ የተፋታ እና ራሱ በጠመቀው ጠላ የሰከረ (elitist and intoxicated with its own ideology) ብለው እንዲህ ያብራራሉ፡፡
‘. . . . . ከ80 በመቶ በላይ አርሶና አርብቶ አደር የሆነውና በትውልድ አካባቢው ተወስኖ
የሚኖረው የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄዎቹ ከማንነት ጋር ብቻ የተያያዙ የብሔርተኝነት ጥያቄ
ሊሆኑ አይችሉም። እንዲያውም አርሶ እና አርብቶ አደሩ ሕዝብ ቋንቋውንና ባህሉን
ከመጠቀም የሚያግደው ማንም አካል ስለሌለ የማንነት ጉዳይ ቀዳሚ አጀንዳው ሊሆን
አይችልም። በአገራችን በሚታየው ዓይነት የአርሶ አደርና የአርብቶ አደር የማሕበረ
ኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሕዝብም ከጅምሩ ብሔርተኛ የመሆን ሥነ-ልቦና ሊኖረው
አይችልም።’
ይህ አስታያት የሚነሳው ማንነትን መዳረሻቸው የደረጉ ጥያቄዎችን ጥልቀት እና ዳርቻ ካለመረዳት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ራስን በራስ ማሰተዳደር ለምሳሌ የማንነት ጥያቄ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን ይህ የዲሞክራሲም ጥያቄ ነው እንጂ ኦሮሞ ስለሆንን ከኦሮሞ የብሄር ማንነት የሚመዘዝ ምሰለኔዎች ያስተዳድሩኝ የሚል አቅላይ(reductionist) ትርጉም ሊሰጠው አይገባም፡፡ ለምሳሌ የወለጋ ህዝብ ራስን በራስ ማስተዳደር ጥያቄዎቹ የተመለሱለት በተጭበረበረ ምርጫ በብልጥግና የተሾሙበት ባለስልጣናት ኦሮሞዎች በመሆናቸው ብቻ እንደሆነ የማሰብ ያህል ነው፡፡ ነገር ግን ይሄ አተያይ ከብልጽግና ላሞኛችሁ የጨዋታ ህግ በምን ይለያል? የወጡበትን ማህበረሰብ መሠረት የደረጉ ፖለቲከኞች መነሻቸው አንድም በሚገባ ልውክልው የምችልው ማህበረሰብ ይሄ ነው ብሎ በመወሰን፤ እንዲሁም የትግል ውጤታማነቴ እውን የሚሆነው በዚህ አካሄዴ ነው ብለው ከማሰብ የሚመነጭ እንጂ የጥያቄቸው ይዘት ቀለም በብህርተኝነት ብቻ የሚገለጽ ሆኖ አይደለም፡፡ እንዲያም ሆኖ ከፊሎቹ በሀገር ደረጃ ያላቸው ምስል የኔነው በሚሉት ማህበረሰብ ላይ የሚያሰፍኑት የመልካም አስተዳደር እና እድገት ጥርቅም (aggregate) ውጤት ነው ብለው ሲያምኑ፤ ሌሎቹም ደግሞ ከማህበረሰባቸው የዘለለ የፖለቲካዊ ህብረት የመመስርት ወይም የማስቀጠል አጀንዳ ራሱ ውይይት፤ድርድር እና ህዝበ ውሳኔ እንዲሰጥበት የሚፈልጉ ናቸው፡፡
ታድያ አቶ ልደቱ ከላይ ተዘረዘሩት ፖለቲካዊ ግቦች መሬት የረገጡ ህዝባዊ ጥያቄዎች አድርገው አይወስዱቸውም፡፡ይልቁንም የዕለት-ተዕለት ኑሮውን የሚፈታተኑና የበለጠ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባ በርካታ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያው ችግሮች ላይ ያላተኮረ በማለት ችግሩን የቅድሚ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባውን ያለማገናዘብ የትግል ኣላማ ልየታ ስህተት ድርገው ይወስዱታል፡፡
ነገር ግን ዲሞክረሲያዊ ብሄርተኞች የወጡበት ገበሬ ሰላም የሌለው፤ ማዳበሪያበጊዜ የማይደረሰው፤ በህክምና ዕጦት የሚቸገረው ራስን በራስ የማስተዳደር ዲሞክራሲያዊ ጸጋ እንዲጠቀም ባለመደረጉ መሆኑን ያምናሉ፡፡ እርግጥ ነው ይህ ዲሞክራሲያዊ ጸጋ ከላይ ያልናቸውን የዕለት-ተዕለት አንገብጋቢ ችግሮቻቸውን ከመፍታት ባሻገር የመረጡት አስተዳዳሪ ቋንቋቸውን የሚናገር ብሎም በሃገራዊው የፖለቲካ አውድ ላይ በልካቸው እንዲወከሉ የሚታገል የሚያግዝ መሪ ይሰጣቸዋል ፡፡ ስለዚህ በዲሞክራሲዊ አግባብ የሚረጋገጥ እራስን በራስ ማስተደደር ብሄርተኞች ወደፊትና ወደኋላ በመግፋት የሚወቀሱባቸውን ጉዳዮች የሚፈታ
በመሆኑ የአቶ ልደቱ ወቀሳ የተጋነነ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
እኔ በግሌ በኦሮሞ ልሂቃን ላይ የሚታየው ድክመት በሶስት ንዑስ ርእሶች ክፍዬ ነው የማየው፡፡ በአንደኛ ደረጃ ሊቀመጥ የሚገባው ችግር ከጥቂት ልሂቃን በስተቀር የኦሮሞ ብሔርተኝነት ጥያቄዎችን በውስጥ ትግልም ሆነ ብሔር ተሻጋሪ በሆኑ መድረኮች ላይ በግልጽ እና በአጭር አገላለጽ ለመበየን ያለመቻል ነው፡፡ ይህ ችግር በውስጥ የአስተሳሰብ ጥራት ጉድለት፤በውጪ ደሞ ትግሉን ሌሎች በአግባበ እንዳይረዱት ብሎም እንሻፈው እንዲበይኑት አድረጓል፡፡ የኦሮሞን የብሄርተኝነት ትግል ለመረዳት ቅርበቱም
አጋጣሚውም የነበራቸው ግለሰቦች ጭምር ‘ምን የቀረ ጥያቄ ኦሮሞ አሁን አለው?’ እያሉ የሚያሽሟጥጡት ጉዳይ ሲሆን ይታያል፡፡ ‘ፊንፊኔ ኬኛ’ በሚለው የአንድ ሰሞን የማጠልሸት ፖለቲካዊ ሩጫ ከኦሮሞ ማህበረሰብ የማይወለዱ ነገር ግን በከተማዋ ውስጥ በላባቸው ንብረት አፍርተው የሚኖሩትን ባለሀገርም ባለመብትም የሆኑ ዜጎችን ንብረት ለመቀማት ያሰፈሰፈ ስግብግብ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ተደርጎ እንዲሳል ሆኗል፡፡ በዚህ ወቅት ኦሮሞ ከተማዬ ከሚላት ፊንፊኔ ምን ምን ነገሮችን እንደሚፈልግ አንደ ሁለት ብሎ ቆጥሮ የማስረዳት ክፍተት ነበረ፡፡ ‘እንዲውም ዘነቦብሽ’ እንደሚባለው የሚፈልገውን ፖለቲካዊ ዓላማ ለማሰፈጸም ጥሩ አምባገነን ያገኘ የመሰለው የቀኝ ዘመሙ ሃይልም ሆነ ጠሚው የተፈጠረውን ውዥንብር በአግባቡ ለራሳቸው ግብ ተጠቅመውበታል፡፡
በዚሁ ርእስ ስር ሊጠቀስ የሚገባው ተያያዥ ጉዳይ በክልሉ የሚኖሩ እና ኦሮምኛ ተናጋሪ ያልሆኑ የሀገሪቱ ዜጎች ላይ ያለውን የጸጥታ እና ደህንንት ጫና እንዴት ፖለቲካው መፍትሄ ሊያበጅለት እንደሚገባ እምነቱንና አቋሞቹን ለማብራራት ያለመቻል ነገር ነው፡፡ ክልሉን የአፈና ቄራ አድርጎ ለመሳል ቀን ከለሌት በሚሰራበት የቀን ተቀን ፕሮፖጋንዳ ውስጥ የግድያ ዜናዎች ብቅ ባሉ ቁጥር ብቻ በማውገዝ በቂ ስራ ተሰርቷል ማለት አይቻልም፡፡ ስለ ወጥ ብሄረ-ክልል መፍጠር ሃሳብ ላይ የሚከሰስበትን ፤ስለዜጎች እንቅስቃሴ፤የከተሞች እድገት ፖሊሲ፤የህዝብ ለህዝብ ግንኑነቶቻና የተፈጥሮ ጥበቃ ጉዳዮች ላይ አቋሞቹን አዋህዶ ወጥ ምስል መፈጠር ነበረበት፡፡
በሁለተኛ ደረጃ የሚቀመጠው ችግር ዲሞክራሲያዊ ባህልን በሚታገሉበትም ሆነ ከዛ ውጪ ባለው ማህበረስብ ማስፈን ቁልፍ የብሄርተኝነትን ጥያቄዎች እንደሚፈታ ካለመረዳት እና ካለማስረዳተ የሚመነጭ ነው፡፡ ለምሳሌ ፊንፊኔ/አዲስ አበባ የባለቤትነት
ጥያቄን እንመልከት፡፡ ከላይ በአንደኛ ደረጃ የተቀመጠውን ጥያቄው የሚቀርብበትን የግልጽነት ችግር ስንሻግር፤ የጥያቄው ተገዳዳሪዎች ሁሉንም የይገባኛል ይዘት አሜን የሚሉት ባይሆንም ከመብራራቱ በፊት እንደሚኖረው ቅዋሜ ሊፈጥር አይችልም፡፡
በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠውን የዲሞክራሲያዊነት ባህል ስንገነባ ማህበረሰባችን የሚገባውን፤ተገዳዳሪያችንም የሚያሰፈልገውን የማያጣበት የሰጥቶ መቀበል አውድ ስለመፈጠሩ እርግጠኛ መሆን ያሰችለናል፡፡ በብልጽግና ፓርቲ ውስጥ ጥቂት ሊባሉ
የሚችሉ ለኦሮሞ ብሔርተኛነት ርዕዮት ሀቀኛ ስሜት ያላቸው ግለሰቦች አይጠፉም፡፡ ብዙ ጊዜ እንደሚታየው እንዚህም ቢሆኑ የኦሮሞ ታሪካዊ ጥያቄ በሚባሉ ጉዳዮች ላይ በአምባገነኖች ‹እኔ እመልስልሃለው› የአቋራጭ ወጥመድ ተጠልፈን የሚወድቁበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡ የኦሮሞ ፊንፊኔ ላይ ያለውን የተብራራ ጥያቄ ከብልጽግናዋ አዳነች አቤቤ ይልቅ በዲሞክራሲያዊ ተዋስዖ በላቀና ዘለቄታ ባለው ሁናቴ ማግኘት ይችላል፡፡ ከአብይ አህመድ አምባገነናዊ አካሄድ ይልቅ በዲሞክራሲያዊ አግባብ ሰጥቶ በመቀበል ሂሳብ የሚጎናጸፈው የባህል ውክልና እኩልነት የሚነጻጸር አይደለም፡፡
በሶስተኛ ደረጃ የማስቀመጠው ችግር የሚወክሉትን ህዝብ ኢኮኖሚዊ ድርሻ በሚመጥን መልኩ በብሄራዊው ምጣኔሃብታዊ ጉዳዮች ላይ የደመቀ የተሳትፎ ውይይት አለማድረጋቸው ሆኖ ይታየኛል፡፡ ምሳሌ ለመንቀስ ያክል በመንግስት ባለቤትነት ባሉ
ድርጅቶች(Satet Owned Entrprises) ሽያጭ ሂደት ላይ ሲብከነከኑ ብዙ አይታዩም፡፡ በጦርነትም ሆነ በአባካኝ የመንግስት እብደት የሚጠፋው ሃብት የሰፊው የኦሮሞ ህዝብ አንጡራ ሃብት መሆኑ እስኪዘነጋ ድረስ በመንግስት ላይ በሚሰነዘሯቸው ትችቶች እንዲ ዓይነት ቀለም ያላቸውን አተያዮች አይካትቷቸውም፡፡ እንዳንዴ ‘ጥጃ ጠባ ሆድ ገባ’ ብላ ላሚቷ የተረተችው በብሄር ምስስሉ ምክንያት ብሄርተኞቹም የሚያስቡት እንዲያ ይሆን ወይ ያስበላል፡፡ 45 ሚሊዮን የሚደርሰውን የክልሉ ህዝብ ከሰሜን አሜሪካ ካናዳን፤ ከደቡበ አሜሪካ አረጅንቲናን ፤ከአውሮፓ ስፔንን ከአፍሪካ የአልጄሪያን ህዝብ እንደሚያክል አስታውሰው የዕድገት ፍላጎታቸውን አያልሙም፡፡ አዳማ እንደ ካናዳ ሁለተኛ ከተማን ቶሮንቶ ወይም እንደ የሰፔኗ ሁለተኛ መዲና ባርሴሎና የምትዘምነው መቼ ነው? ብለው ሲያስቡ ብዙ አላጋጠሙኝም፡፡ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ያለው ዜሮ የባቡር መስመር
ዝርጋታ እንደ ሰፔን 16ሺህ ወይም እንደ አህጉራችን እፍሪካዊቷ አልጄርያ 4ሺህ የሚደርሰው መቼ ነው? ሲሉ አይሰማም፡፡ ከ200ሺ ተማሪዎች በታች በዓመት ተቀብሎ የሚስተምረው የክልሉ የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ መቼ ነው በህዝብ ብዛት
ከሚመጣጠነው አርጀንቲና እኩል 2.5 ሚሊዮን ተማሪዎችን የሚያስተናግደው? ማለት የነጠረ ብሔርተኝነት አይሆንም ወይ ያስብለኛል፡፡ ‘በእኔ ጊዜ የአዲስ ዩኑቨርሰቲዎችን ግንባታ አትጠብቁ’ የሚለው ጠቅላይ ሚኒስትር፤ የተቀበላቸውን ተማሪዎች የምግብ
እጥረት ዜና የሆነበት አስተዳዳር፤ በክልሉ የተንሰራፋው በትምህርት ተወዳዳሪ ያለመሆን ጉዳይ፤የድንቁርና መስፋፋት ብሄርተኞችን ለምን እንቅልፍ አይነሳም?
ከላይ የጠቃቀስኳቸውን እና ሌሎችም የሚያነሷቸውን ተገቢ ትችቶች ያረመ ብሄርተኝነት አዲስ ሰም እንስጠው ካልን ዲሞክራሲያዊ ገንቢ ብሄርተኝነት (Democratic Constrctivist Ethnonationlism) ሊባል ይችላል፡፡ ይህ ብሔርተኛ የኔ የሚለውን ህዝብ፤ቋንቋውን ባህሉን፤ጋራውን፤ሸንተረሩን ይወዳል፡፡ የኦሮሞ ህዝብ መጻኢ-ተስፋው የሚጨልመው የሆነ ንጉስ ሃውልት በሰም ተቀርጾ በቤተመንግስት በመቀመጡ ወይ ባለመቀመጡ ሳይሆን ቀጣዩ የኦሮሚያ ተረካቢ ትውልድ የገቢሳ እጄታን ስኬት በሚደግም ዓለም-አቀፋው የትምህርት ተወዳዳሪነት ላይ እንዳይገኝ ሆኖ በጦርነትና በድንቁርና እንዲማቅቅ ሲፈረድበት ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊ ገንቢ ብሄርተኝነት (Democratic Constrctivist Ethnonationlism) ሁሉም ብሄር ያስፈለገዋል-ኢትዮጵኒሰቱም ጨምሮ፡፡
ወቀሳውን እንደዘረዘርን ሁሉ የኦሮሞ ብሄርተኞች ሊመሰገኑበትም የሚችል ጥቂት ነገሮችን ማንሳት እዚህ ጋር የግድ ይላል፡፡ አቶ ልደቱ ለምንም ኣይነት ርዕዮተ-ዓለም ምንገዴ የሆነውን ብልፅግናን እዚሁ ከረጢት ውስጥ ከተው ካላጣጣሉት በቀር፤ የኦሮሞ ብሔርተኞች ትግራይ ህዝብ ላይ የተከፈተውን ጦርነት በአንድ ልብ በሚባል ደረጃ ተቃውመውታል፤አጋርነታቸውንም
አሳይተዋል፡፡ አሁን በአማራ ክልል ላይ የሚደረገውን ነገር ትክክል አለመሆኑን ለመናገር ሲደነቃቀፉ አይታዩኝም፡፡ ይህ መልካም ጎናቸው ከሞራል ልዕልና የሚነሳ ሳይሆን በተግባር ማዕከላዊ መንግስትን የሚቆጣጠሩ ስብስቦች ህዝቦች ላይ የሚያደርሱትን ጭቆና ገፈት ቀማሽ በመሆን ስሜቱን ስለሚገነዘቡት ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በበጎ ሊጠቀስ የሚገባው ነገር ቁጥሩ አመርቂ ባይሆንም መንግሰትን፤ተቃዋሚውን እንዲሁም አማጺውን ለመግራት በብሔር መመሳሰል ሃቅ የማየምታታበት ብዙ ምሁርም በዚህ የብሔርተኛ ስብስብ ውስጥ መኖሩ የማይካድ ነው፡፡ እንደ በቴ ኡርጌሳ ያሉ በሳል ብሔርተኛ፤ በውይይት የሚያምን ዴሞክራት ስብዕናዎችንም ያየነው ከዚሁ መንደር ነው፡፡ በማስፈራርያም በጥቅምም ሳይደለል አምባገነንነትን
መሃል ከተማ በቁም እስር ሆኖ የሚታገለው የዳውድ ብሔርተኛው ኦነግ ነው፡፡ በዚሁ ሁሉ ወቀሳ ማኻል አቶ ልደቱ እንደ ዘበት ብሔርተኝነት የራሱ የሆነ ጠንካራ ጎን የለውም ማለት አይደለም ብለው የዘለሉትን እውነት በተወሰነ መልኩ ላብራራ፡፡ ንዑስም እንበለው ዐብይ ብሄርተኝነት በአግባቡ ከተገራ ዜጎችን በሀገር,ዓቀፍም ሆነ አነስ ባለ የኢኮኖሚ አሃድ ውስጥ አነቃቅቶ ላቅ ያለ አበርክቶዎት እንዲሰጡ ያግዛል፡፡ ይህ ከውስጥ የሚመነጭ ለወጡበት ህብረተሰብ የሚኖር ተቆርቋሪነት ሳይገደብ አወንታዊ ግቦች ላይ አተኩሮ ከዲሞክራሲያዊ አስተሳሰቦች ጋር ተዋህዶ ከጎለበተ እድገትን የሚያሳልጥ የማህበራዊ ታዳሽ ሃይል ነው ቢባል
ማጋነን አይሆንም፡፡
እንደኢትዮጵያ ያሉ በብሄር ጥያቄን መዕከላዊ የፖለቲካ ማታገያ ማገዶም ሆነ ልምምድ ባላቸው ሀገሮች፤ ከመዋቀራዊነት እናውርደው በሚል በደማቁ ነፍስ ዘርቶ የሚንቀሳቀስን አስተሳሰብ ለማዳፈን የሚከፈት ዘመቻ ምን ያክል እንደሚሳካ ባይገባኝም፤ ዴሞክራሲያዊ ሂደት እስከተከተለ ድረስ ግን ዘውዳዊውንም አገዛዝ ለማምጣት የሚደረግ ሰላማዊ ትግልን ካለፍርሃት ለማስተናገድ ሆደ ሰፊ መሆን ከኦሮሞ ብሔርተኞች የሚጠበቅ ልእልና ነው፡፡ የዚህን ንዑስ ርዕስ ዋና ሃሳብ የሚጠቀልል ምስል በጥያቄ መልክ ከዚህ በታች እንዲህ ተመላክቷል፡፡
አቶ ልደቱ በዋና ተዋናይነት ካነሱዋቸው አካላት መሃል የኦሮሞ ብሔርተኞች ላይ ለይቼ መፃፌ እንደ ማሳያ ግምገማው እንደምን ቢደረግ እውነተኛ ጠቃሚና ትክክለኛ ሊሆን እንደሚችል ለማሳያነት ተጠቀምኩበት እንጂ በተቀሩትም የተጠቀሱ ብሔርተኝነት አራማጆችም ተመሳሳይ መከላከል ሊደረግባቸው እንደሚችል አምናለሁ፡፡ ዓላማዬ ብሔርተኝችን መከላከል ሳይሆን ርዕዮታቸው ላለንብት ምስቅልቅል ቀጥተኛ አበርክቶት መጋነኑን ለማሳየት ብቻ ነው፡፡
2.2.3.የልደቱን ተዋንያን ለመነሻነት በተዘጋጀው ምድብ ቢታዩ
ከዚህ ቀደም እንደተባለው የተዋናይነት ዝርዝር አካታችነት ላይ (compreshensiveness) እና አንፃራዊ ድርሻዎቻቸው(relative contributing factor) አከራካሪ ሊሆን እንደሚችል ለመጥቀስ ሞክሬ ነበር፡፡ ይሄኛውን መነሻ ያሳየሁት አንድ ወዳጄ ወታደሩን ከተጠያቂዎቹ አንዱ አድርገህ ስታበቃ እጁን በደረቱ ላይ አድርጎ የወንድማማቾችን ጦርነት የፋፋመውን ህዝብ ለምን ረሳህው
ብሎ ጠይቆኛል፡፡ በተወሰነ የአክስዮን ድርሻ መግባት ነበረበት እላለሁ በምልሰት ሳስበው፡፡